በጆር ወረዳ ኡንጎጊ ቀበሌ የተገነባውን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ህንፃ እንዲሁም የመንገድ ዳር የገበያ ሼድ ተመርቀዋል።
በጋምቤላ ክልል የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ገለፁ።
ርዕሰ መስተዳድሯ በቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት በጆር ወረዳ ኡንጎጊ ቀበሌ የተገነባውን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ህንፃ እንዲሁም የመንገድ ዳር የገበያ ሼድ መርቀዋል።
ከጋምቤላ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት (መጋቢት 22/2017 ዓ.ም)
ርዕሰ መስተዳድሯ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ በዚህ ወቅት እንዳሉት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ምቹ የትምህርት አካባቢን መፍጠር ወሳኝ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻልና ተፈላጊውን የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ላደረገው ድጋፍ አመስግነው ሌሎች አካላትም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የክልሉ መንግስትም ያሉትን እጥረቶች ለመፍታትና ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት እንዲሰጥ ለማስቻል የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በፕሮጀክቱ የተገነባው የመንገድ ዳር መገበያያ ሼድ የህብረተሰቡ የገበያ ትስስር እንዲያድግ እና የተለያዩ ቦታዎች ሲገበያዩ ለነበሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ምቹ ሆኔታን የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል።
የጆር ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኡሞድ ኡቦንግ እንደገለፁት በወረዳው ተሰርተው የተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች በተለይም ትምህርት ቤቱ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው የመንገድ ዳር የገበያ ሼዱ ደግሞ ህብረተሰቡ አንድ አካባቢ ላይ እንዲገበያይ የሚረዳ ነው ብለዋል።